ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ሪፎርም ለደንበኞች ጥራት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው – አገልግሎቱ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ሪፎርም ለደንበኞች ጥራት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው አለ።
አግልግሎቱ ያደረገውን የፖሊሲ እና አሰራር ማሻሻያ ስራ አስመልክቶ ከመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር እንዳሉት÷ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ሪፎርም ለደንበኞች ጥራት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው።
ማሻሻያው ስኬታማ መሆን እንዲችል የመገናኛ ብዙኃን ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።
በአገልግሎቱ የጥራትና ፕሮሰስ ማኔጅመንት ስራ አስፈፃሚ እሱባለው ጤናው በበኩላቸው÷ ያልተቆራረጠ ኃይል ተደራሽ ለማድረግና በቂ ገቢ ለመሰበሰብ ማሻሻያው አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ማሻሻያው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ አገልግሎቱ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በቅርበት ይሰራልም ነው ያሉት።
የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎቱ ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የሚያደረገውን ጥረት እንዲያግዙም ጠይቀዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ተወካዮች አገልግሎቱ ቴክኖሎጂን የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራቸው የሚገኙ ነፃ የስልክ የጥሪ እና ዳታ ማዕከል ጎብኝተዋል።
በኤፍሬም ምትኩ