ጦርነትን በትንሽ ኪሳራ በድል የሚወጣ ሠራዊት እየተገነባ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጦርነትን ሳይዋጋ ከሩቅ የሚያስቀርና ከተፈጠረም በትንሽ ኪሳራ በድል የሚወጣ ሠራዊት እየተገነባ ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡፡
የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በመደበኛ ኮርስ ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በተገኙበት አስመርቋል፡፡
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የኮሌጁን አቅም ከዚህ በላይ ለማጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የመከላከያ አመራሮች የዘመኑን የቴክኖሎጂ እድገትና ስልጣኔ የሚመጥን አቅም በመላበስ ሠራዊቱን በተገቢው መንገድ መርቶ ወደ ድል ማብቃት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ሠራዊት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ፥ የዛሬ ተመራቂዎች በጥናትና ምርምር ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባት፣ ለውጥን በተግባር ማሳየትና አካባቢን መቃኘት ይኖርባችኋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በንግግራቸው ፥ ሠራዊቱ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ አቅሙን እያስመሰከረ ኢትዮጵያን አሻግሯል ነው ያሉት።
የቀጣናውን ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው መንገድ መገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ሠራዊቱ የባሕር በርን ጨምሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽዖ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም መንግስት ፊቱን ወደ ልማት በማዞር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እያሳካ የሀገሪቷን ከፍታ እያረጋገጠ ቀጥሏል ያሉ ሲሆን ፥ የሠራዊቱ አመራሮች ሕዝቡን የሚጠቅም የልማት ሥራዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ጦርነትን ሳይዋጋ በሩቁ የሚያስቀርና ከተፈጠረም በትንሽ ኪሳራ በድል የሚወጣ ሰራዊት እየተገነባ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ እና መራኦል ከድር