Fana: At a Speed of Life!

የሐኪሞች ጥያቄ የፖለቲካ ኪሳራ በገጠማቸው ሰዎች መጠለፉ ትክክል አይደለም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛ የጤና ባለሙያዎች ለምን የደመወዝ ጥያቄ አነሱ ብሎ የሚያስብ ሰው አለ ብዬ አልገምትም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት እንዳሉት÷ የሕክምና ሙያ የተከበረ እና የሰዎችን ሕይወት የሚታደግ ነው፡፡

መንግስት እና ማሕበረሰቡም የሕክምና ባለሙያዎች ለዜጎች የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ በቅጡ እንደሚረዱ አንስተዋል፡፡

በሕክምና ባለሙያዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች ትክክል ሆነው ጥያቄዎች የሚቀርቡበት መንገድ ስህተት ከሆነ ግን የተፈለገውን ውጤት እንደማያስገኝ አመልክተዋል፡፡

“እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ሐኪሞች ለምን የደመወዝ ጥያቄ አነሱ ብሎ የሚያስብ ሰው አለ ብዬ አልገምትም“ ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የጤና ዘርፉን ችግር ለመፍታት ጤናማ መንገድ ካልተከተልን ችግሩ ይባባሳል እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ የሚቀርቡ የደመወዝ፣ የጥቅማ ጥቅም፣ የቤት እና መሰል ጥያቄዎች የባለሙያዎች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ የመፍትሄ መንገዱ ግን ከባለሙያዎች ወጥቶ በሌሎች እጅ ተጠልፏል ብለዋል፡፡

ጉዳዩ ደመወዝ ወስደው በማያውቁ ሰዎች እና መሰረታዊ አገልግሎት ሰጥተው በማያውቁ ሰዎች መጠለፉንም አብራርተዋል፡፡

እንቅልፍ አጥተው የሰዎችን ሕይወት የሚታደጉ ሐኪሞችን ትክክለኛ ጥያቄ ጉዳዩን በቅጡ የማያውቁ ሰዎች ከጠለፉትና የራሳቸው አጀንዳ ማስፈጸሚያ ካደረጉት ጉዳዩ አላማውን እንደሳተ ይቆጠራል ነው ያሉት፡፡

በዘርፉ የሚነሳውን ጥያቄ በሶስት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል አንስተው÷ ይሄም ትክክለኛ ሐኪሞች በቅንነት ኑሮ ከብዷቸው ያነሱት፣ የፖለቲካ ኪሳራ የገጠማቸው አካላት ያነሱት እና ሐኪም መሳይ ጋወን ለባሽ ፖለቲከኞች ያነሱት ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ሐኪም መሳይ ጋወን ለባሽ ፖለቲከኞች የትክክለኛ ሐኪሞችን ጥያቄ በመጠቀም የተከበረውን ሙያ እንዳጠለሹት አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም መሰል ሁኔታዎችን ማጣራት እንደሚገባ ጠቁመው ÷ ለዚህም ሁሉም የጤና ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች ጥያቄያችሁን በስሜት ሳይሆን በምክንያትና በስሌት ማስላት ስትጀምሩ ተቆንጥሮም ቢሆን ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ሰው ለማዳን ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍሉ ሐኪሞች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ አውስተው÷ ለእነዚህ መሰል ሐኪሞች ለጥያቄያቸው ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ሐውልት መቆሙን አንስተዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.