Fana: At a Speed of Life!

ኢራን ኳታር በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ፈጸመች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ኳታር በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽማለች፡፡

ጥቃቱን ተከትሎ በዶሃ ከፍተኛ ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን÷ በኳታር የሚገኘው እና አሉዴይድ የተሰኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር በጥቃቱ ኢላማ ተደርጓል፡፡

በሀገሪቱ የአሜሪካ ኤምባሲ የአሜሪካ ዜጎች ወደ መጠለያዎች በመግባት ራሳቸውን ከጥቃት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርቧል፡፡

“የአሸናፊነት መልካም ዜና” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጥቃቱ አሜሪካ በሶስት የኢራን ኒውክሌር መሰረተ ልማቶች ላይ ለፈጸመችው የአየር ጥቃት የተሰጠ አጸፋ እንደሆነ የኢራን ጦር መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከኢራን የተተኮሱ ስድስት ሚሳኤሎች በኳታር ሰማይ ሲምዘገዘጉ ታይተዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የአጸፋ ጥቃት መከላከል የሚያስችል የመካከለኛው ምስራቅ የብሔራዊ ደህንነት ቡድን እያቋቋሙ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ ኢራን በኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ጥቃት የፈጸመች ሲሆን÷ በባህሬን ኩዌት የጥቃት ማስጠንቀቂያ ሳይረን ድምጾች አየተሰሙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከጥቃቱ በኋላ የኢራን ጦር በሰጠው መግለጫ÷ የጦር ሰፈሩ የአሜሪካ አየር ሃይል በምዕራብ እስያ ለሚያደርገው ዘመቻ ዋና ማዘዣጣቢያ ሆኖ ያገልግል ነበር ብሏል ፡፡

ኢራን የጦር ሰፈሩን ለማጥቃት የተጠቀመቻቸው ስድስት ቦምቦች አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ከፈጸመቻቸው ስድስት ቦምቦች ጋር ተመሳሳይ ቁጥር አላቸው፡፡

የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ÷ ኢራን በሀገራቸው በሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሠፈር ላይ የፈጸመችውን ጥቃት በጥብቅ አውግዟል፡፡

ጥቃቱ የኳታርን ሉዓላዊነት፣ አየር ክልልና ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ መሆኑን ገልጿ÷ አስፈላጊው አጸፋዊ ርምጃ ይወሰዳል ሲል አስጠንቅቋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.