የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በምርጥ ሥራ አመራር የወርቅ ተሸላሚ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በ10ኛው የአፍሪካ ሲቪል ሰርቪስ ቀን በምርጥ ሥራ አመራር የተመራ ተቋም ሽልማትን በማሸነፍ የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል።
10ኛውን የሲቪል ሰርቪስ ቀን አስመልክቶ ከአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የመንግስት ተቋማት በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት ዋናው መስሪያ ቤት አውደርዕይ አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም በሪፎርሙ የታጠቃቸው ቴክኖሎጅዎችና ለሕብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በአውደርዕዩ ላይ አቅርቧል፡፡
ተቋሙ በምርጥ ሥራ አመራር የተመራ ተቋም ሽልማትን በማሸነፍ የወርቅ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ውድድሩ አራት ዘርፍ እንደነበረው ገልጸው፥ የፌዴራል ፖሊስ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት በሚለው ዘርፍ አሸናፊ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ የወርቅ ዋንጫ በመሸለሙ ለፌዴራል ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ጭምር ኩራት መሆኑን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው፥ ሽልማቱ ተቋሙን ይበልጥ ጠንክሮ እንዲሰራና ሀገርን የሚያኮሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የሚያበረታታው ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን የሚያግዝ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነር ጄነራሉ፣ በቀጣይ አዳዲስ ነገሮችን ለሀገርም ለአህጉርም ለማስተዋወቅ ይሰራል ብለዋል፡፡
በታሪኩ ለገሰ