በኦሮሚያ ክልል የወተት ምርት ገበያ ትስስርን ሥርዓት ለማስያዝ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የወተት ምርት የገበያ አቅርቦት ትስስርን ሥርዓት ለማስያዝ እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷የወተት ምርት ገበያ ትስስርና የእንስሳት መኖ ዋጋ መናር ለወተት ምርት ውጤታማነት አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡
ገበያ ላይ ያለው የእንስሳት መኖ ዋጋ እና ጥራቱን የጠበቀ የወተት ዋጋ እንደማይመጣጠን ጠቅሰው ÷ የገበያ ሰንሰለቱም ወጥነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ም/ሃላፊ ቶሌራ ደበላ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷በክልሉ ያለውን የወተት ምርት አቅርቦት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል 12 የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ የዘርፉን ገበያ ትስስር ሥርዓት ለማስያዝ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በወተት ገበያ ትልቁ ችግር ሕገ ወጥ ንግድ መሆኑን ያስረዱት አቶ ቶሌራ ÷ ይህም የወተት ጥራትን ዝቅ ከማድረግ ባለፈ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንደሚቀንስ አንስተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት የቴክኒክ እና ቁጥጥር ቡድን ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ÷ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚመረተው የወተት ምርት ለገበያ እንዲቀርብ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ሰማ በበኩላቸው÷ ነዋሪዎች የሚያነሱት ቅሬታ ተገቢ ነው፤ የወተት ዋጋን ለማሻሻል ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም በቂ መፍትሄ አልተገኘም ብለዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታትም ሕገ ወጥ ደላላዎችን ከገበያ ከማስወጣት ጀምሮ ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
በሲፈን መገርሳ