Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ዛሬም እንደ ትናንቱ በትጋት ይሠራል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ዛሬም እንደ ትናንቱ በትጋት ይሠራል አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ መንግስት ዛሬም የሰላም በሮችን ክፍት አድርጎ እየጠበቀ የሕዝቡን የሰላምና የልማት ጥያቄ ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የአማራ ክልል ሕዝብ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መክፈል የማይገባዉን ውድ ዋጋ በጥቂት ጥቅመኞች ምክንያት እየከፈለ ይገኛል፡፡ የፋኖን ታሪካዊ አነሣሥ እና ዓላማ ባልተከተለ አግባብ ራሳቸዉን በፋኖ ስም የሚጠሩ ፅንፈኛ ኃይሎች በቀሰቀሱት ግጭት የአማራ ክልል ሰላም እና ልማት ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ ፋኖ ሀገር በባዕድ ወራሪ እጅ በወደቀችበት እና ማእከላዊ መንግሥት በግዞት በቆየበት ወቅት ሀገርን ለማዳን የተደረገ ተጋድሎ የተመራበት ድንቅ ስያሜ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን የሀገሩን እና የክልሉን መንግሥት ለማፍረስ እና የባዕዳንን ተልእኮ ለማሳካት የተደራጁ ቡድኖች መጠሪያ ተደርጎ ሀገርን እና ሕዝብን ውድ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ታዳጊዎችን ከትምህርት ገበታ ነጥሏል፡፡ ሕዝብን ከለማት እንቅስቃሴዎች አሰናክሏል።

የአማራ ክልል ሕዝብም የግጭት ጠማቂዎቹን እና የተላላኪዎቹን አጀንዳ በሚገባ ተገንዝቦ መንግሥት ሰላም እንዲያሰፍን በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን በተለያዩ አግባቦች ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብ ክልሉን ከግጭት እና ሥርዐት አልበኝነት ለማውጣት በየአካባቢዉ ተሰባስቦ ምክክር እና ውይይት አካሂዷል፤ የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በአጀንዳነት እንዲያዙ አድርጓል፤ ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራዉ ቡድን ትክክለኛ የነፃነት ታጋይ መስሎት የተቀላቀለ ወጣት ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ እንዲመለስ በሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለምኗል፡፡

ከዚህም መሳ ለመሳ የፌደራል የፀጥታ ተቋማት እና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር የክልሉን ሰላም ለማረጋጥ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ መሥዋዕትነትም ከፍለዋል፤ እየከፈሉም ነው፡፡ በዚህም በክልሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች ሰላም ማስፈን ተችሏል፡፡ በተፈጠረው አስቻይ ሁኔታም የክልሉ ሕዝብ ከልማት ጥረቶች ወደ ኋላ እንዳይቀር በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

ይሁን እንጅ በፀጥታ ኃይላችን ጥረት እና በሀገር ሽማግሌዎች ተማፅኖ አንጻራዊ ሰላም ቢሰፍንም ሕዝቡ በሚሻዉ ልክ የክልሉ ሰላም ሙሉ ለሙሉ አልተረጋገጠም፤ የዜጎች እንቅስቃሴ ከእገታና ዘረፋ ስጋት በምልዓት አልተላቀቀም፡፡ የነገ ሀገር ተረካቢዎች በተሟላ መልኩ ወደ ትምህርት ገበታ አልተመለሱም፡፡ የልማት እንቅስቀሴዎች ሕዝብ እና መንግሥት በሚሹት ልክ እንዲፋጠኑ ምቹ ድባብ አልሰፈነም፡፡ በዚህ ምክንያት ሕዝቡ ብሶቱን ለመንግሥት ጎላ አድርጎ ለማሰማት በተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችን አካሂዷል፡፡

በሰላማዊ ሰልፎቹ መንግሥት የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ ልማትን እንዲያጠናክር ሕዝቡ ጠይቋል፡፡ መንግሥት የውስጥ ባንዳዎችን እና የውጭ ኃይሎችን አደብ እንዲያስገዛለት፣ ልጆቹ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱለት፣ ማሳውን ወደ መጎልጎልና ማረስ እንዲሰማራ፣ በኑሮው በሰላም ወጥቶ መግባት እንዲችል ምቹ ድባብ እንዲፈጠርለት፣ ሰላሙን በጋራ ለመጠበቅ እንደተዘጋጀ እና መንግሥት ሕግ ለማስከበር የጀመረዉን ጥረት በፅናት እንደሚደግፍ በሰላማዊ ሰልፎቹ ገልጿል፡፡

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ግጭቶችን ለማስወገድ በርካታ አማራጮችን ሲከተል መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ጥያቄ ያላቸዉ አካላትን በማቅረብ ለማነጋገር እና ለመደራደር በርካታ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ በተደጋጋሚ የይቅርታ እና ምሕረት ጥሪዎችን አቅርቧል፡፡ በዚህም በርካታ በስሕተት የጥፋት ኃይሎችን ተቀላቅለዉ የነበሩ አካላት እጃቸዉን በመስጠት ሕይወታቸዉን አትርፈዋል፤ ሕዝቡን ለመካስ የሚያስችል የተሐድሶ ሥልጠናም አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ጥቂት ጥቅመኞች የሕዝቡን ሰላም እያወኩ የባዕዳንን ተልእኮ ለማሳካት እየተወራጩ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት የሕዝቡን የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ዛሬም እንደትናንቱ ዝግጁ ነው፤ መንግሥታዊ ኃላፊነቱም ነው፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ ከክልሉ ሕዝብ፣ ከክልሉ አስተዳደር እና የፀጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት መንግሥት የላቀ ጥረት ያደርጋል፡፡ ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ሰላሙን ለመጠበቅ ያሳየዉን ቁርጠኝነትም ያደንቃል፡፡

የሰላም በሮችን ዛሬም ክፍት አድርጎ እየጠበቀ የሕዝቡን የሰላም እና የልማት ጥያቄ ለመመለስ ከመቸዉም ጊዜ በላቀ ደረጃ ዝግጁ መኾኑንም መንግሥት ያረጋግጣል፡፡ የሰላም አማራጮችን የማይቀበሉ አካላትን በክልሉ የፀጥታ መዋቅር እና በፌደራል መዋቅር አማካኝነት አደብ በማስገዛት የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ይሠራል፡፡ ሕዝቡ በአደባባይ ያቀረባቸዉን ጥያቄዎች ከሕዝብ ጋር ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡ ሕዝቡ በሠለጠነ አግባብ ሐሳቡን በመግለጹም መንግሥት ምስጋና ያቀርባል፡፡

ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ/ም

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.