በመዲናዋ የካንሰር ቅድመ ምርመራን ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የጡት እና የፕሮስቴት ካንሰር ቅድመ ምርመራ እና ሪፈራል አቅምን ማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።
“ክሊኒተች” የተሰኘው ዲጂታል ማጣሪያ ፕሮጀክት በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች የሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙዎች መረጃዎችን በቀላሉ እንዲሰበስቡ ያስችላል፡፡
ተጋላጭነትን ለማሰስ እና ፈጣን ጥቆማዎች እንዲሰጡ የሚያግዘው ፕሮጀክቱ÷ ስፒሪት ሄልዝ በተሰኘ ድርጅት መዘጋጀቱ ተመላክቷል፡፡
ፕሮጀክቱ በአስትራ ዜኒካ፣ በግሎባል ሄልዝ ፓርትነርሺፕ እና በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የሚተገበር ሲሆን÷በኢትዮጵያ የከፍተኛ ደረጃ የካንሰር ምርመራ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያለመ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የአስትራዜኒካ ፕሬዚዳንት ዲፓክ አሮራ÷ ድርጅታቸው በአፍሪካ በጤና ፕሮግራሞች ላይ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ከምርመራ ባለፈ አዳዲስ መድኃኒቶችን በማስተዋወቅ እና የካንሰር ሕክምና ክትትልን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፋት እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የካንሰር ሕክምና አገልግሎትን ለማሻሻልና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
የትሮፒካል ሄልዝ ኤንድ ኤዱኬሽን ትረስት የኢትዮጵያ ሃላፊ ዶ/ር ዮሴፍ ማሞ በበኩላቸው÷ በከተማም ሆነ በገጠር ነዋሪዎች እንደ ካንሰር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በማህጸን በር ካንሰር የተመዘገቡ ስኬቶችን መነሻ በማድረግ የጡት እና የፕሮስቴት ካንሰር ሕመምተኞችን ልየታ ማስፋፋት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በዘርፉ የዲጂታል አሰራር ሥርዓትን መተግበር የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ጫና ማቃለል ያስችላል ነው ያሉት።
የፕሮጀክት መክፈቻው በአዲስ አበባ የሚገኝ የፕሮጀክቱ ፓይለት ጤና ጣቢያን መጎብኘት ያካተተ ሲሆን÷ የዲጂታል ካንሰር ምርመራን ከኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ጋር ለማዋሃድ ስምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል፡፡
ኢኒሼቲቩ በፈጠራ ቴክኖሎጂ እና በጠንካራ ትብብር ታግዞ ሕመሙን አስቀድሞ በመለየት በበሽታው ምክንያት የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ የሚያስችል አቅምን እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡