Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሀገራት በኢነርጂ መሰረተ ልማቶች እያስተሳሰረች ነው – የአፍሪካ ሕብረት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተሳሰር ለኢነርጂ ነጠላ ገበያ ትግበራ መሰረት እየሆነች ነው አለ በአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽን፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ’’የኢነርጂ ነጠላ ገበያ ሁኔታ ግምገማ፣ ተቋማዊ ማሻሻያና የመመሪያ አቀራረብ’’ በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የአፍሪካ ነጠላ የኤሌክትሪክ ገበያ አጀንዳ ከፍተኛ የቴክኒክ ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡

በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ዳይሬክተር ካሙጊሻ ካዛውራ ÷ በፈረንጆቹ በ2021 በተካሄደው የሕብረቱ ጠቅላላ ጉባዔ የአፍሪካ የኢነርጂ ነጠላ ገበያ ትግበራ ፍኖተ ካርታ መቀመጡን አስታውሰዋል።

የዘንድሮው ከፍተኛ የቴክኒክ ስብሰባም የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 የኢነርጂ ነጠላ ገበያ የዕቅድ የአፈፃጸም ትግበራ ሒደት ግምገማ የሚደረግበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢንርጂ ኮሚሽንም የልማት አጋሮችን በማስተባበር የአህጉሪቷን በኢነርጂ መሰረት ልማት ለማስተሳሰር እየሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡

የአህጉሪቷ አባል ሀገራትም የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ትስስርን በማሳለጥ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ጅቡቲና ቀሪ ጎረቤቶቿ ጋር ከፈጠረችው የሃይል ትስስር በተጨማሪ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት ቀጣናን በኤሌክትሪክ ሃይል እያስተሳሰረች ነው ብለዋል።

ይህም ለአፍሪካ ሕብረት የኢነርጂ ነጠላ ገበያ ትግበራ አቅም እየሆነች መምጣቷን እንደሚያሳይ ነው የገለጹት፡፡

በአውሮፓ ሕብረት ልዑክ የፖሊሲና የትብብር ክፍል ኃላፊ ጂያንሉካ አዞኒ በበኩላቸው÷ በአውሮፓ አፍሪካ የአረንጓዴ ኢነርጂ ልማት ተነሳሽነት መርሕ የአህጉሪቷን የሃይል ልማት እየደገፈ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ የኢነርጂ ፋይናንስ መፍትሔዎች፣ የፖሊሲና ደንብ ዳይሬክተር ዋሌ ሾኒባሬ ÷ የአፍሪካ ልማት ባንክ አህጉሪቷን በኤሌክትሪክ ሃይል በማስተሳሰር ልማቷን እንድታሳልጥ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የዘርፉ የስራ ሃላፊዎችና ሙያተኞች እንዲሁም የልማት አጋርና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሥራ ሃላፊዎችና ተወካዮች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.