ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም በማዋል የተጠረጠሩ 24 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም በማዋል የተጠረጠሩ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምርታማነት ማሻሻያ ልህቀት ማዕከል ዲንን ጨምሮ 24 ግለሰቦች ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ ፍሬው አመነ በምርታማነት ማሻሻያ ልህቀት ማዕከል ዲን፣ ተፈሪ ፈይሳ የማዕከሉ ምክትል ዲን እና ኢንተርፕርነርሺፕ አሰልጣኝ፣ ሀይማኖት አቡን በማዕከሉ ምክትል ዲን፣ ወ/ሮ አሊማ መሃመድ ፋይናንስ ዳሬክተር፣ ሶስና መሃመድ ግዢ ዳይሬክተር እና እንግዳ ወንድአፍረሽ የኦዲት ዳይሬክተርን ጨምሮ 24 ናቸዉ።
1ኛ ክስ በ1ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 8ኛ፣ 9ኛ፣ 10ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9 (1) (ሀ) እና (2) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ለማስገኘት እና በመንግስት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ የሚል ነው።
1ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ያለ ክፍያ መሰጠት ያለበት ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የሚሰጥ ስልጠና፤ በተቋሙ የሚሰጡ ስልጠናዎች ያለ ክፍያ መሰጠት ያለበት መሆኑን የሚገልፀውን የአሰራር መመሪያ በመተላለፍ 3ኛ ተከሳሽ አበል ክፍያ እንዲፈፀም በደብዳቤ በመጠየቅ፣ 1ኛ ተከሳሽ ክፍያውን በመፍቀድ በማፅደቅ ከ459 ሺህ ብር በላይ ወደ 11ኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር በማስተላለፍ ለግል ጥቅማቸዉ ያዋሉ እና ያለአግባብ የስልጠና አበል ክፍያ የከፈሉ በመሆኑ።
1ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች የስልጠና አበል 200 ሺህ ብር ወደ 11ኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ በማስተላለፍ ለግል ጥቅማቸዉ ያዋሉ ሲሆን ያለአግባብ የስልጠና አበል ክፍያ በመክፈል 1ኛ፣ 4ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች፣ 8ኛ ተከሳሽ የክፍያ ሂሳብ በማዘጋጀት በመመሪያ መሰረት ሁሉም ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟላበት ሁኔታ እና ሊከፈል የማይገባዉ ክፍያ 300 ሺህ ብር እንዲከፈል በማድረግ፣ በ4ኛ ተከሳሽ የክፍያ ሂሳብ ፈቃጅነትና አረጋገጭነት እንዲሁም በ1ኛ ተከሳሽ ክፍያን በማፅደቅ 143 ሺህ ብር ያለአግባብ የውሎ አበል ክፍያ እንዲፈፀም ያደረጉ በመሆኑ።
በአጠቃላይ ተከሳሾች የተቋሙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በመሆናቸዉን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በግልፅ ተግባር በመተላለፍ ከተቋሙ ባንክ ሂሳብ ቁጥር በድምሩ 2 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ወደ ራሳቸዉ እና የተለያዩ አካላት ባንክ ሒሳብ በማስተላለፍ ለግል ጥቅም በማዋል እና በዚሁ ልክ በማዕከሉ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆናቸዉ፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
በሁለተኛ ክስ በተመሳሳይ በ1ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ተከሳሾች በማዕከሉ በኃላፊነት እና ሰራተኝነት ተመድበው በሚሰሩበት ወቅት የማዕከሉን የአሰራር መመሪያ በመተላለፍ ወደ ማዕከሉ ገቢ መደረግ ያለበትን የአገልግሎት ክፍያ በድምሩ 4 ሚሊየን 750 ሺህ 790 ብር ወደ ግለሰቦች እና ወደ ራሳቸው የባንክ ሂሳብ ገቢ ማድረጋቸዉ በክሱ ተዘርዝሯል።
3ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ 4ኛ፣ 6ኛ፣ 9ኛ፣ 13ኛ፣ 14ኛ፣ 15ኛ፣ 16ኛ፣ 17ኛ፣ 18ኛ፣ 19ኛ እና 21ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን፤ ተከሳሾች የመንግስትን መመሪያ በመተላለፍ ከተቋሙ ባንክ ሂሳብ ቁጥር በተለያዩ ጊዜያት 11 ሚሊየን 447 ሺህ 304 ብር ወደ ራሳቸዉ እና የተለያዩ አካላት ባንክ ሒሳብ በማስተላለፍ የማይገባ ጥቅም በማግኘት፤ በማስገኘት እና በዚሁ ልክ መንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆናቸዉ፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
4ኛ ክስ በ1ኛ፣ 2ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ያለ ገቢ ደረሰኝ ገንዘቡን በመቀበል ለሁሉም ሰልጣኞች ኦርጅናል ሰርተፍኬት በመስጠት ማዕከሉ ለሰጠው አገልግሎት ሊሰበሰብ የሚገባውን ገንዘብ ባለመሰብሰብ እና የተሰበሰበውንም በመመሪያው አግባብ በደረሰኝ ገቢ ያላደረጉ በመሆናቸው በዚህ ልክ በመንግስት ላይ ጉዳት ያደረሱ በመሆኑ።
የተቋሙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሆነው ሲሰሩ የአሰራር መመሪያውን በመተላለፍ ለተቋሙ ገቢ ሊደረግ የሚገባውን ገንዘብ ገቢ አለማድረግ እና ወጪ ሊሆን የማይገባውን ወጪ በማድረግ ወደ የተለያዩ አካላት ባንክ ሒሳብ በማስተላለፍ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆናቸዉ፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 7ኛ፣ 12ኛ፣ 20ኛ፣ 21ኛ፣ 22ኛ፣ 23ኛ እና 24ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበው 5ኛ ክስ ደግሞ የተቋሙ ማኔጅመንት አባላት ሆነዉ ሲሰሩ የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለማስገኘት እና በመንግስት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ወጪን ለመቀነስ የተዘጋጀ የአፈጻጸም መመሪያ በመተላለፍ ለአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሰጥ በመወሰን 80 ሺህ ብር 1ኛ ተከሳሽ የግዢ ወጪ በማዘዝ፤ 4ኛ ተከሳሽ የግዢ ወጪን በማረጋጋጥ እና ማፅደቅ፤ 7ኛ ተከሳሽ የግዢ ወጪ ሂሳብ በመስራት በግለሰቦች ሂሳብ ገቢ በማድረግ ለግል ጥቅም እንዲውል በመደረጉ እንደሆነ ተብራርቷል።
ተከሳሾቹ በአጠቃላይ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብን ለግል ጥቅማቸዉ በማዋል ነዉ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዩች ችሎት ክስ የተመሰረተባቸዉ።
በሲፈን መኮንን
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!