Fana: At a Speed of Life!

40 የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ተሰጣቸው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጥራት ቁጥጥር እና አደጋ አስተዳደር የሰለጠኑ 40 የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ተሰጣቸው፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ጋር በመተባበር ለባለሙያዎች በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጥራት ቁጥጥርና በአቪዬሽን አደጋ አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና መስጠቱን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

ተቋሙ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ስራዎችን በበላይነት ለመምራት በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፥ ስልጠና የወሰዱ 40 ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጿል፡፡

የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ከ12 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አሰራሮች ላይ ባደረገው ኦዲት ሀገራችን ምንም ዓይነት የሴኪዩሪቲ ስጋት እንደሌለባት ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም አገልግሎቱ የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ጋር በተፈጠረው መልካም ግንኙነትና ትብብር ስልጠናው ከዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በመጡ ባለሙያዎች ከሰኔ 9 እስከ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰጥቷል፡፡

ከዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የመጡት አሰልጣኞች እንዳሉት፥ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀቱ አየር መንገዱ ተደራሽ በሚሆንባቸው ሀገራት ሁሉ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ የጥራት ቁጥጥር ተግባራትን ለማካሄድ የሚያስችል ሲሆን፥ ባለሙያቹ ስልጠናውን በስኬት ማጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

ስልጣኞች ያገኙት ዕውቀት ተቋሙ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመፈፀም የሚያስችል ከመሆኑም ባለፈ፥ ሀገራችን ለአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ዘርፍ እየሰጠች ያለችው ልዩ ትኩረት ጉልህ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም ነው አገልግሎቱ የገለጸው፡፡

አገልግሎቱ በመረጃው የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጠንካራ የጥራት ቁጥጥር ትግበራና የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ዝግጁነት የድርጅት አባል ሀገራት ኃላፊነት መሆኑን ገልጾ፥ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ደኅንነት በአለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጿል፡፡

በስልጠናው የተገኘውን ዕውቀት፣ ክህሎት እና የአስተሳሰብ ለውጥ በቀጣይ በአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ለተያዘው ራዕይና አጠቃላይ ተቋማዊ ስትራቴጂ ግብዓት አድርጎ በማዋል የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተመራጭነት ይበልጥ በማሳደግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.