Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ ቤተ መንግስትን ጨምሮ በመዲናዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ከጎበኙ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ፥ በአገልግሎት ዘርፉ የተከናወኑ ሥራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በአገልገሎት ዘርፍ 8 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንዲያመጣ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
የአገልግሎት ዘርፉ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት፣ ቴሌኮሙኒኬሽን እና ንግድን እንደሚያካትት ጠቅሰው፥ እነዚህም ለግብርናና ለኢንዱስትሪ አስፈላጊ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን በሚመለከት በተከናወኑ ሥራዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉን ገልጸው፥ በዚህ ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን እንደጎበኙ ተናግረዋል፡፡
ይህም በኢሚግሬሽን የሪፎርም ሥራዎች፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በኮሪደር ልማት፣ በመዳረሻ ቦታዎችና በሆቴሎች ላይ በተሰሩ ስራዎች የተገኘ ውጤት እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
በመዲናዋ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች የአንድነት እና ፍሬንድሺፕ ፓርኮችን፣ የሳይንስ ሙዚዬምና ብሔራዊ ቤተ መንግስትን መጎብኘታቸውን ጠቁመው፥ ከዚህም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአንድነት እና ፍሬንድሺፕ ፓርኮች እንዲሁም የሳይንስ ሙዚዬምን 13 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች እንደጎበኙት አብራርተዋል፡፡
ለጎብኝዎች ቁጥር መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ዘርፎች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዱ መሆኑን አንስተው ፥ በዚህ ዓመት ተጨማሪ 13 አውሮፕላኖችን በመግዛት አጠቃላይ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር 180 አድርሷል ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት ስድስት አዳዲስ መዳረሻዎችን በመጨመር የመዳረሻዎቹን ቁጥር 136 ማድረሱንና ከ19 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን ማጓጓዙን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የባቡር ኮርፖሬሽን ገንዘብ ማመንጨት የማይችልና የሰራተኞቹን ደመወዝ መክፈል የማይችል እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ አቅሙን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች በገቢ እና ወጪ ንግድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም በቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ለተገኘው ውጤት የባቡር ኢንዱስትሪው ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቡና የወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.