Fana: At a Speed of Life!

“ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” መጽሐፍ ዋነኛ ዓላማ ለትውልድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማስረከብ ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) “ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” መጽሐፍ ዋነኛ ዓላማ ከትናንት በመማር ለቀጣዩ ትውልድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማስረከብ ነው አሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)።

በተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የተጻፈ “ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” መጽሐፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ተመርቋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች ተገኝተዋል።

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያዊያን በዓለም ላይ አስደናቂ ባህል፣ ወግ፣ እሴትና ጥበብ ያለን ማህበረሰቦች ነበርን፤ ነን ብለዋል።

ይህ አስደናቂ የኢትዮጵያዊያን ፍልስፍና ዓለም አቀፋዊ አለመሆን ውስጣዊ ጥያቄ ፈጥሮባቸው መቆየቱን ጠቅሰው፤ ይህ ጥያቄ ለመጽሐፉ መወለድ መነሻ ምክንያት እንደሆናቸው አንስተዋል።

ሁላችንንም ለወግና ማዕረግ ያበቃችን ኢትዮጵያ ያልተረዳንላትና ያላወቅንላት መሰረታዊ ጉዳይ ሌላኛው የመጽሐፍ መነሻ ሃሳብ ነው ብለዋል።

እንደሀገር ያለፍንባቸው መንገዶችና ያልተቀሰሙ ትምህርቶች፣ ትናንት የባከኑና ያመለጡ ዕድሎች ምንነትም በመጽሐፉ ተዳስሷል ነው ያሉት።

የተፈጠሩ መሻኮቶችና የመከኑ ትውልዶች፣ ባለመግባባትና ባለመወያየት የጨለሙ ተስፋዎች ምክንያትና ምንነት በመጽሐፉ እንደተመላከቱም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ እንደዘበት የዘነጋቻቸው ጥበቦችና ዕውቀቶች ለሀገር አቅም አለመሆናቸው መጽሐፉ የሚዳስሳቸው ጉዳዮች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተፈጠረው ምቹ ሀገራዊ ድባብ በመንግስትና ፓርቲ ስራ የሚሰሩ አካላት ብቻ ሳይሆን ምሁራን መፃፍ፣ መነጋገር፣ መወያየትና ለሀገራዊ ጉዳዮች ሃሳባቸውን የሚያዋጡበት ምህዳር መፈጠሩም ለመጽሐፉ ውልደት አንዱ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የካበተ ዕውቀትና እሴት እያለ እንደሌለ መቆጠሩን አስታውሰው፤ ለኢትዮጵያዊ ጥያቄና ምላሾች በዜጎቿ እጅ እንጠቀም የሚል ሀገራዊ ፍልስፍና እና እሳቤን በማሰላሰል መወለዱንም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዚሁ ፍልስፍና እና እሳቤ ግንባር ቀደም መሪ በመሆን መጽሐፉ እንዲወለድ ሆኗል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መጽሐፉ የውስጥን ቁጭትና ምኞት፣ የተስፋና ምናብ ጉዞዎችን፣ በግላቸውና እንደማህበረሰቡ የተመጣበትና የቀጣይ ጉዞ መንገድ ላይ የኢትዮጵያን ዕውነት ለመግለጽ ምልከታና አረዳዳቸውን ያሳረፉበት መሆኑን ገልጸዋል።

ዋነኛ ዓላማውም ከትናንት በመማር ዛሬና ነገን የተሻለ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማስረከብ መሆኑን አስረድተዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.