ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡ ሥራዎች ላይ በማተኮር እየሰራ ነው አሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ገጠር ክላስተር አስተባባሪ አዲሱ አረጋ።
በአዳማ ከተማ አስተዳደር 171 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
ዛሬ ከፕሮጀክቶቹ መካከል የዶሮና የወተት ላሞች እርባታ ማዕከላት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የአዳማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህንፃና የአስተዳደር ህንፃዎች፣ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያና መልሶ መጠቀሚያ ማዕከል፣ የመኖ ማቀነባበሪያ እንዲሁም የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ይገኙበታል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት አቶ አዲሱ አረጋ፤ የማንሰራራት ዘመን ላይ ሆነን የማይቻሉ የሚመስሉ የልማት ፕሮጀክቶችን እውን እያደረግን ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ ፍጥነትና ጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እየበቁ መሆኑን ጠቅሰው፣ የክልሉ መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለአገልግሎት ክፍት ከማድረግ ባለፈ አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ሥራ ጎን ለጎን እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከድህነት ለመውጣት የሚደረገው ርብርብ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሀይሉ ጀልዴ በበኩላቸው÷ የነዋሪውን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማዋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ዘዴ በመደገፍ ከወረቀት ነፃ የሆነ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፤ 122 አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል ገብተው ከ30 በላይ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ጠቁመዋል።