Fana: At a Speed of Life!

አረንጓዴ አሻራ የአፈር መሸርሸርን በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ አስችሏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አረንጓዴ አሻራ የአፈር መሸርሸርን በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስና ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጥናት አመላከተ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ለምግብ ዋስትና፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋምና የደን ሽፋን እንዲያድግ ማስቻልን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ መጥቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ አሳሳቢ የነበረውን የአፈር መሸርሸር በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ እንዳስቻለ ግብርና ሚኒስቴር በቅርቡ ያወጣው ጥናት አመልክቷል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፥ አረንጓዴ አሻራ ከመጀመሩ አስቀድሞ በየአመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ለም አፈር ተጠርጎ ወደ ወንዞች እና ሀይቆች ይገባ ነበር፡፡

እንደ አጠቃላይ በሀገሪቱ 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ቶን አፈር ከእርሻ እና ከግጦሽ መሬት እንዲሁም ከከተማ አካባቢ እየተጠረገ ወደ ወንዞች እና ወደ ግድቦች ሲገባ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

ይህም ለም አፈርን እንዲሟጠጥ በማድረግ ምርታማነትን ከመጉዳቱም ባሻገር የአፈር ማዳበሪያን ከውጭ በማስገባት ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉን ነው የገለጹት፡፡

ሆኖም ባለፉት አመታት በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት የአፈር መሸርሸር ምጣኔ እየቀነሰ መምጣቱን ማየት እንደተቻለ ጥናቱን ዋቢ አድርገው አስረድተዋል፡፡

አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አስቀድሞ በደለል ይወሰድ የነበረውን በዓመት በአማካይ 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ቶን አፈር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ አሁን ላይ ወደ 208 ሚሊየን ቶን ዝቅ እንዲል አስችሏል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.