Fana: At a Speed of Life!

አረንጓዴ አሻራን ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ጋር የማስተሳሰር ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በበጋ ወቅት ሲከናወኑ ከቆዩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ጋር በማስተሳሰር በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በየካ ተራራ በመገኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አመራር አባላትና ሰራተኞች ጋር አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሃይ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ዜጎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞችና አመራር አባላት በመርሐ ግብሩ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን አንስተው፥ በመርሐ ግብሩ 100 ሺህ ችግኞችን የመትከል እቅድ መያዛቸውን ተናግረዋል።

የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በተከነወኑባቸውና ከዚህ ቀደም በባህር ዛፍ ተሸፍነው በነበሩ ስፍራዎች መካሄዱም ነው የተገለጸው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከዛሬ ባሻገር የነገ ትውልድ ስንቅ መሆኑን በማውሳት፥ ከዚህ አኳያ ሁሉም ዜጋ በየአካባቢው በንቃት በመሳተፍ አሻራውን እንዲያኖር ጥሪ አቅርበዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በበጋ ወቅት ሲከናወኑ ከቆዩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ጋር በስፋት እንዲተሳሰሩ መደረጉን ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፥ ከዚህም ውስጥ ወደ 2 ሚሊዮን ሄክታር በሚጠጋው መሬት ላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደሚከናወን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከናወነ ባለው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ይተከላሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.