Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አፍሪካውያንን ለተሻለ ዕድገት ያነሳሳል – ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ  

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ  ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አፍሪካውያንን ለተሻለ እድገት ያነሳሳል አሉ።

ኮሞሮስ ባቀረበችው ግብዣ መሰረት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ 50ኛው የኮሞሮስ የነፃነት በዓል በሞሮኒ ከተማ ሲከበር መታደማቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ለግብዣው ምስጋና አቅርበው፥ ኢትዮጵያ ከኮሞሮስ ጋር ያላትን  የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን ለመቻል ባደረገችው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቷን አብራርተው÷ ኮሞሮስ በግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ትልቅ ተሞክሮ ልትወስድ እንደምትችል አመላክተዋል፡፡

የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ  በበኩላቸው፥ የፕሬዚዳንት ታዬ በበዓሉ መታደም ኢትዮጵያ ለኮሞሮስ ያላትን ክብር ያሳያል ብለዋል።

ከፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጋር  በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይትን ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አፍሪካውያንን ለተሻለ እድገት የሚያነሳሳ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ለውጥ ማሳያ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድም ኮሞሮስን ከተቀረው ዓለም ጋር በማስተሳሰር ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ መገልፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.