ዘንድሮ ለችግኝ ተከላ ከተለዩ ቦታዎች ውስጥ 750 ሺህ የሚሆኑት ጂኦግራፊያዊ መገኛቸው ይመላከታል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብርና ሚኒስቴር ዘንድሮ ለችግኝ ተከላ ከተለዩ ቦታዎች ውስጥ 750 ሺህ የሚሆኑት ጂኦግራፊያዊ መገኛቸው ይመላከታል አለ፡፡
በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ ፋኖሴ መኮንን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፥ በዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ይሸፈናል፡፡
በትናንሽ መሬት ላይ በአርሶ አደሮች በጓሮ ከሚተከሉት ችግኞች ውጪ የግለሰብ፣ የመንግስት ወይም የማህበራት የጂኦግራፊያዊ መገኛ ቦታቸውን በሚያመላክት ቦታ ላይ ይተከላሉ ብለዋል፡፡
በመሆኑም ከ750 ሺህ በላይ የሚሆኑ የችግኝ መትከያ ቦታዎች ጂኦግራፊያዊ ማመላከቻ እንዳላቸው ገልጸው፥ ለእያንዳንዱ የተከላ ቦታ አንድ ሪፖርተር በመመደብ ለዚያ ቦታ ከተመደበው የችግኝ ቁጥር በላይ በሲስተሙ መመዝገብ እንደማይቻልም አስረድተዋል ፡፡
ችግኞችን የጂኦግራፊያዊ መገኛ ቦታቸውን በሚያመላክት ቦታ ላይ መትከል የሀሰት ሪፖርትን ከማስቀረት ባለፈ መርሐ ግብሩን የሚያጣጥሉ አካላት እውነታውን እንዲገነዘቡት ለማድረግ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም ማንኛውም ሰው ጎግል ማፕ ላይ በመግባት መረጃውን ማግኘት እንደሚችል አስገንዝበዋል።
በዘንድሮ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ሙሉ በሙሉ የጂኦግራፊያዊ መገኛ ቦታቸውን በሚያመላክት ቦታ ላይ እንደሚተከሉም ገልጸዋል።
በመሳፍንት እያዩ