Fana: At a Speed of Life!

የሁቲ አማጺያን ያገቷቸውን የመርከብ ሰራተኞች እንዲለቁ አሜሪካ አሳሰበች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሁቲ አማጺያን ያገቷቸውን የመርከብ ሰራተኞች በአፋጣኝ እንዲለቁ በየመን የአሜሪካ ኤምባሲ አሳስቧል።

በቀይ ባህር ላይ ስትንቀሳቀስ በሁቲ አማጺያን የሮኬት ጥቃት የተፈጸመባትን መርከብ ሰራተኞች ህይወት ለመታደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል።

አማጽያኑ በመርከቧ ላይ ባደረሱት ጥቃት እስካሁን ቢያንስ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአውሮፓ የባህር ኃይል ተልዕኮ አስታውቋል።

በዚህ ሳምንት ብቻ ተመሳሳይ ጥቃት ሲደርስ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አስታውሶ፤ አሁን ጥቃት የደረሰባት መርከብ 25 ሰራተኞችን መያዟን ገልጿል።

እስካሁን ሶስት የመርከቧ ሰራተኞች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ስድስት ሰዎችን መታደግ እንደተቻለ የአውሮፓ የባህር ኃይል ተልዕኮን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

ቀሪ የመርከቧ ሰራተኞች በአማጺያኑ ሳይታገቱ እንዳልቀረ የገለጸው በየመን የአሜሪካ ኤምባሲ፤ አማጺያኑ በአፋጣኝ ሰራተኞቹን እንዲለቁ አሳስቧል።

በግሪክ ኩባንያ የተሰራችው ኢተርኒቲ ሲ የተባለችው መርከብ የላይቤሪያ ሰንደቅ ዓላማ ስታውለበለብ ነበር።

የፊሊፔንስ ባለስልጣናት 21 የመርከቡ ሰራተኞች የፊሊፒንስ ዜግነት እንዳላቸው በመግለጽ ቀሪዎቹ ሩሲያዊያን ናቸው ብለዋል፡፡

በአቤል ንዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.