Fana: At a Speed of Life!

በቪዛ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጪ ዜጎች ከተሰጣቸው ቀነ ገደብ ካለፉ ቅጣት ይጠብቃቸዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በቪዛ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የየትኛውም ሀገር ዜጎች ከተሰጣቸው ቀነ ገደብ ካለፉ ቅጣት ይጠብቃቸዋል አለ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው የዓመቱን ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት እና ሳምንታዊ ክንውኖችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በቀጣዮቹ ሳምንታት በአዲስ አበባ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን በብቃት ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባዔ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 እንዲሁም እስከ 25 ሺህ ተሳታፊዎች ይስተናገዱበታል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በጳጉሜን ወር እንደሚስተናገድ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ጉባዔዎቹን ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ ለማስተናገድና ተሞክሮዎቿን ለማካፈል በዝግጅት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ሊከተሉ የሚገባቸውን ጥንቃቄ በተመለከተ መልዕክት ያስተላለፉት ቃል አቀባዩ፤ በትምህርት እና በጉብኝት ቪዛ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሰጣቸውን ጊዜ እንዳያሳልፉ አስገንዝበዋል።

ቀነ ገደቡን የሚያሳልፉ አካላት በተደረገው የህግ ማሻሻያ መሰረት ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስረድተዋል።

በቪዛ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የየትኛውም ሀገር ዜጎች ከተሰጣቸው ቀነ ገደብ ካለፉ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የገለጹት አምባሳደር ነብያት፤ ቅጣቱ ህጉን ተላልፈው የሚገኙ የኢትዮጵያ መኖሪያ መታወቂያ ካርድ የሌላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም ያካትታል ነው ያሉት።

በአሸናፊ ሽብሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.