ኢትዮጵያ የምታስተናግደው ሁለተኛ የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በሚገባ ሊተዋወቅ ይገባል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን ሁለተኛ የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ አስቀድመው ማስተዋወቅ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
“ከራዕይ ወደ ተግባር: የኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የፓናል ውይይት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የምግብ ዋስትና በግለሰብ፣ በማህበረሰብ እና በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት እየሰራበት ይገኛል።
በምግብ ስርዓት ሽግግር ከምርት እስከ ተጠቃሚ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ሁሉን አቀፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ለምግብ ስርዓት ሽግግር የአሰራር ማዕቀፎች አዘጋጅታ በመተግበሯ ውጤቶች ተገኝቷል ነው ያሉት።
ይህንንም ተሞክሮ ኢትዮጵያ በዓለም መድረኮች እያቀረበች እንደምትገኝ አንስተው፤ ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄዱ ሀገሪቱ ለምግብ ስርዓት ሽግግር ላከናወችው ስራ እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ጉባኤውን አስቀድመው ሊያስተዋውቁ እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላችው፤ እንደ ሀገር ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የምግብ ሉዓላዊነትን በሁለንተናዊ ሁኔታ ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ እና ጣልያን የጋራ አዘጋጅነት የሚካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።