በ67 ሚሊየን ብር በባምባሲ ከተማ የተገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባምባሲ ከተማ በ67 ሚሊየን ብር የተገነባው የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ለአገልገሎት ተዘጋጅቷል።
የክልሉ ውኃ መስኖና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋዝ የባምባሲ ከተማ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በከተማውና አካባቢው የሚገኙ ከ35 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለ20 ዓመታት የውኃ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
አራት ጥልቅ ጉድጓዶች፣ ከ500 ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃ ማጠራቀም የሚያስችሉ የተለያዩ የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖችና ከ32 ኪሎ ሜትር በላይ የውኃ መስመሮች ተመቻችተውለት ለአገልግሎት መዘጋጀቱም ተመልክቷል።
በፕሮጀክቱ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በክልሉ ከዚህ ቀደም ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅ ችግር እንደነበረባቸው አንስተዋል።
ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር አለመኖር፣ የተቋራጮች እቅም ማነስና የበጀት እጥረት ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መሠረት በማድረግ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በወቅቱ የተጠናቀቀውን የባምባሲ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክትን ለአብነት አንስተዋል።
ይህ ውጤት ያልተመቻቸው አካላት በየአካባቢው ግጭት በማስነሳት ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ጥረት እያደረጉ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከጥፋት ኃይሎችና ከወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ራሱን ሊጠብቅ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።