Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ ቀናት በበርካታ አካባቢዎች የክረምቱ ዝናብ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣዮቹ ቀናት የክረምቱ የዝናብ መጠን በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየሰፋ እና እየጠነከረ ይሄዳል አለ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፡፡

ኢንስቲትዩቱ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ ÷ በተያዘው ሐምሌ ወር የክረምት ዝናብ በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እየሰፋ እና እየጠነከረ የሚሄድ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተሻለ ዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖር አመልክቷል፡፡

በዚህ መሰረትም ደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን፣ መካከለኛው፣ ምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ያገኛሉ፡፡

ስለሆነም እርጥበታማው የአየር ሁኔታ በተለይም በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየተስፋፋ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያስተናግዳሉ፡፡

በተጨማሪም በመካከለኛው፣ በሰሜን ምስራቅና በምስራቅ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ፣ መካከለኛው እና ምዕራብ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ስለሚኖር አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡

የሚጠበቀው እርጥበት ለግብርና ሥራ እንቅሥቃሴ አዎንታዊ ሚና ቢኖረውም ስጋቶችን ለመቀነስና የሚኖሩትን መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም የቀረቡትን ቦታ ተኮር የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦች በተገቢው ሁኔታ መተግበር ይገባል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአብዛኛው ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸውና በተለይም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶች እና አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የወንዞች ከፍታ መጨመር ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተመላከተው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሐምሌ 13 ጀምሮ ባሉ ተከታታይ 11 ቀናት በሁሉም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት አከባቢዎች ይበልጥ እንደሚጠናከር ተጠቁሟል፡፡

በተለይ በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን እና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ነጎድጓዳማ እና ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ኢንስቲትዩት አስገንዝቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.