Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የት/ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፡፡

የቢሮው የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ አምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል፡፡

በም/ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ያለፈውን የትምህርት ዘመን ክፍተቶች በቀጣዩ ዓመት ለማካካስ የሚያስችል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አዲሱን የትምህርት ሥርዓት ታሳቢ ያደረገ የመምህራን አቅም ግንባታ፣ የት/ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና የተማሪዎች ምገባ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረትም ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት ከዚህ ቀደም ያቋረጡትንና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን በመመዝገብ ያለፉትን ዓመታት ሊያካክስ የሚችል ሥራ እንደሚከናወን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በ2018 የትምህርት ዘመን ከሰባት ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር በማቀድ ዝግጀት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም የትምህርት ማሕበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.