Fana: At a Speed of Life!

የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባሕል ይበልጥ ሊጎለብት ይገባል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ለማሳለጥ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን የመጠቀም ባሕልን ይበልጥ ማጎልበት ይገባል አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር)።

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ያዘጋጀው 2ኛው ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፍቷል።

አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ንቅናቄ የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ለማዘመን፣ ምርትና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማጎልበት ያለመ ነው።

የንግድ ሳምንቱ የሀገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥና በመግዛት በኩል ለማሕበረሰብ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።

የንግዱ ማሕበረሰብም የንግድ ፍቃድ አውጥቶ በሕጋዊ መንገድ በመስራት የዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲሻሻልና በዘመናዊ አሰራር እንዲካሄድ የራሱን እገዛ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው÷ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያዩ ያስችላል ብለዋል።

የንግዱ ማሕበረሰብ የንግድ ሥራውን በሕጋዊ መንገድ ብቻ በማከናወን በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ የሚያበረክተውን ወሳኝ ድርሻ ይበልጥ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለማቃለል ግብር ኃይል በማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝና በዚህም አምራችና ሸማቹን በቀጥታ ማገናኘት ተችሏል ያሉት ደግሞ የከተማዋ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.