ለሽብር ተልዕኮ የተመለመሉ 82 የአይ ኤስ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሽብር ተልዕኮ የተመለመሉ 82 የአይ ኤስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፥ በፑንትላንድ የሚንቀሳቀሰው የአይ ኤስ የሶማሊያ ክንፍ በተለያዩ ሀገራት እንዲሁም በኢትዮጵያ ለመስፋፋትና የሽብር ቡድኑን ሴሎች ለመመስረት የሚያደርገውን ጥረት በተመለከተ የመረጃ ስምሪትና ጥናት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በተለይም በኢትዮጵያ የሽብር መረብ ለመዘርጋት የሚያደርገውን ሙከራ በተመለከተ ከጅምሩ በመረጃና በማስረጃ ተደግፎ ጥብቅ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱንም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡
የሥጋት ደረጃውን በተመለከተ በየጊዜው ባከናወናቸው ግምገማዎች ተጋላጭነትን የሚያስከትሉና ወደ ብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት የሚያድጉ ተጨባጭ ግኝቶች መለየታቸውንም ጠቁሟል፡፡
የተከናወነውን ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ የማጠናቀር ሂደት ተከትሎ የሽብር ቡድኑ በፑንትላንድ አሰልጥኖ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሰማራቸው 82 ተጠርጣሪዎች ተለይተው ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ከቡድኑ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውና ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች መካተታቸውን የጠቀሰው መግለጫው፥ በተለይ በዓለምአቀፍ የሽብር ቡድኑ በመረጃ ክንፍ የተደራጁ እንዲሁም በፋይናንስና በሎጀስቲክ እገዛ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል፡፡
የሽብር ቡድኑ የጥፋት ተልዕኮውን ለማስፋፋትና ምልመላ ለማከናወን የሃይማኖት ተቋማትንና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን እንደሚጠቀምም ነው አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው ያመለከተው፡፡
የሕዝብን አንድነትና ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ ብሎም ለአመጽና ሁከት የሚያነሳሱ አስተምህሮዎችን ለማስፋፋት ሙከራ ሲደረግ እንደነበር በተጨባጭ ማስረጃ መረጋገጡንም አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ፣ አዳማ፣ ሃሮማያ፣ ሻሸመኔ፣ ባሌ፣ጅማና ሻኪሶ ከተማ ዙሪያ እንዲሁም በአማራ ክልል ከሚሴ አካባቢ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞንና ሃላባ ቁሊቶ ከተማ፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማና በሐረሪ ክልል በቁጥጥር ውለዋል፡፡
ግለሰቦቹን ለመያዝ በተደረገው ስምሪት በየአካባቢው የሚገኘው ኅብረተሰብ ከደኅንነትና ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ያሳየው ተሳትፎ በመልካም አርዓያነት የሚጠቀስ ነው ብሏል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በመግለጫው እንዳስታወቀው፥ በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የሽብር ቡድኑ አባላት ላይ የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ኅብረተሰቡም በየአካባቢው ሰላምን የሚያደፈርሱና ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት አንደ ሁልጊዜው ለሚመለከታቸው የደኅንነትና የጸጥታ አካላት ጥቆማውን በማቅረብ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ አገልግሎቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡