Fana: At a Speed of Life!

ከ134 ሺህ ተማሪዎች በላይ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን በበይነ መረብ ወስደዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 የትምህርት ዘመን 134 ሺህ 828 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን በበይነ መረብ ወስደዋል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፡፡

ከሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሰጥ የቆየው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና በትናንትናው ዕለት ተጠናቅቋል፡፡

የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ በአጠቃላይ 608 ሺህ 742 ተማሪዎች መውሰዳቸው ተመላክቷል፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን 134 ሺህ 828 ተማሪዎች በበይነ መረብ መፈተናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም አጠቃላይ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች 23 ነጥብ 2 በመቶውን እንደሚሸፍን አብራርተው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በወረቀት እንደተፈተኑ ጠቁመዋል።

በበይነ መረብ በአራት ዙር እንዲሁም በወረቀት በሁለት ዙር የተሰጠው ፈተና ከስርቆት እና ኩረጃ ነጻ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡

ፈተናው በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተቋቋሙ 216 የመፈተኛ ማዕከላት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በሰለሞን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.