ህዳሴ ግድቡ ሲጠናቀቅ በዓመት አንድ ቢሊየን ዶላር የሚገመት ገቢ ያስገኛል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ከ66 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ብርሃን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቴክኒካል ኮሚቴ አባል በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ግድቡ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል በመሸጥ በዓመት ወደ አንድ ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ያስገኛል።
ይህ ገቢ ለሀገራዊ በጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው ያሉት።
ከዚህ በተጨማሪም በግድቡ አማካኝነት የተፈጠረው ሐይቅ የጣና ሀይቅን እጥፍ ቦታ የሚሸፍን መሆኑን አንስተው፤ ይህም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ከ254 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ባለው ሐይቁ ላይ መጠናቸው ከ5 ሄክታር በላይ የሆኑ 78 ያህል ደሴቶች በመፈጠራቸው ውሃን መሰረት ያደረገ የቱሪዝም መስህብ ይሆናሉ ሲሉ አብራርተዋል።
ቱሪዝሙ በምላሹ በውስጡ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ከማስቻሉ ባሻገር አዳዲስ ከተሞች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም እንዲስፋፉ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
የግድቡ የኃይል ማመንጫ ክፍል መሠረተ ልማት ግንባታ በተያዘለት ግዜ ተጠናቅቋል ብለዋል።
የቀሩት ሥራዎች የሚያስፈልጋቸው ግብዓት በሙሉ በስፍራው የደረሰና የመገጣጠም ሥራ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
በሄኖክ በቀለ