የብልፅግና ፓርቲ መመስረት ለሀረሪ ክልል ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ መመስረት ሀረሪ ክልልን ከኋልዮሽ ጉዞ በመግታት ዕድገት እንዲመዘገብ አስችሏል አሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በሀረሪ ክልል በዘጠኙም ወረዳዎች የተገነቡ የፓርቲ ጽ/ቤቶችን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ እንደሀገር ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ለዚህም የአመራሩና የህዝብ አንድነት የፈጠረው የመደጋገፍ ዕሴት ወሳኝ ሚና እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘጠኙም ወረዳዎች በመፍጠር፣ በመፍጠንና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ የተገነቡ ህንፃዎች የፓርቲውን የፕሮጀክት አመራር ስርዓት በተግባር የገለጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው እንደሀገር የተመዘገቡ ታላላቅ ሀገራዊ ድሎች የብልፅግና ፓርቲ ፖሊሲዎች ትክክለኛነትና ህዝባዊ ቅቡልነት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
የህዝቡን የልማት ጥያቄ በመመለስ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፥ በኮሪደር ልማት መርሐ ግብር ለሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ የሚሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
በተስፋዬ ሀይሉ