Fana: At a Speed of Life!

የሀረሪ ክልል የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀረሪ ክልል የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ ባለፉት 6 አመታት በህዝብ ቁርጠኝነት እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በርካታ ውጤት አምጥቷል።

የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ምርታማነት እንዲጨምር እና የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን በመቋቋም ረገድ ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሆነ አንስተዋል።

እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ለማረጋገጥ የተጀመረውን ሀገራዊ ግብ በማሳካት ረገድ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራን ፋይዳ በመገንዘብ ችግኞችን መትከል እና በዘላቂነት መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ሁሉም ተሳትፎ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ማውረስ ይገባል ነው ያሉት።

የክልሉ ምክልት ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሮዛ ኡመር በበኩላቸው፤ የተተከሉ ችግኞች ባለቤት እንዲኖራቸው በማድረግ ከተተከለው ውስጥ 82 በመቶውን ማፅደቅ ተችሏል ብለዋል።

ዘንድሮ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለአፈርና ውሃ ጥበቃ የሚያግዙ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኞች በክልሉ እንደሚተከሉ ተናግረዋል።

”በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ በድሬ ጠያሬ በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የምስራቅ ዕዝ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በተስፋዬ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.