Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ የ2017 እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 እቅድ ውይይት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 ዓ.ም እቅድ ውይይት መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት፤ ዓመቱ የእቅዳችንን 95 በመቶ ያሳካንበት ነው ብለዋል።

በዚህም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የተመለሱበት፣ ከ15 ሺህ 900 በላይ ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁበት፣ በኮሪደር ልማት የከተማዋን ውብ ገፅታ ያላበስንበት እና ምትክ ቦታዎችን ለማህበረሰቡ የሰጠንበት ነው ብለዋል።

አክለውም ኢንዱስትሪዎች ያለባቸውን ችግር በመቅረፍ ምርታማነትን በመጨመር ተኪ ምርቶችን ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

የማህበረሰቡን የኑሮ ጫና እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ምርቶች በተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲገቡ፣ በተለያዩ የገበያ አማራጮች እንዲቀርቡ ከማድረግ ባለፈ ዜጎች አምርተው እንዲጠቀሙ አድርገናል ሲሉ ተናግረዋል።

ሁሉንም ታሳቢ ያደረጉ የልማት ሥራዎች መተግበር መቻሉን ያነሱት ከንቲባዋ፤ በ2017 በጀት ዓመት ጥሩ የገቢ አሰባሰብ ውጤት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

ከተሰበሰበው ገቢ 71 በመቶ የሚሆነው ለዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ መዋሉንም አብራርተዋል።

በቅድስት አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.