ከ121 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የዋካ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን በ121 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የዋካ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በሆስፒታሉ ምረቃ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በየአካባቢው የጤና ተቋማት መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ ማድረግ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ ነው።
የጤና ተቋማት መገንባታቸው የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በእጅጉ ያግዛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አገልግሎት አሰጣጣቸው የተሟላ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ለሆስፒታሉ ግንባታ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ እንዲጠናቀቅ መደረጉን ገልጸው፥ ሕብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሆስፒታሉ የተጓደሉ ቁሳቁሶችን በማሟላት ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው፥ የሆስፒታሉ መገንባት በክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሽፋንን 36 ነጥብ 1 በመቶ ማድረሱን አንስተዋል፡፡
ሆስፒታሉ ማህበራዊ ብልጽግናን ያረጋገጠና የህብረተሰቡን ጤና ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፥ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችልም በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
የዋካ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለ100 ሺህ ዜጎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የሺዋስ ዓለሙ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
በአድማሱ አራጋው