የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት የምንሰራቸውን ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት አመት የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት የምንሰራቸውን ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2018 በጀት አመት እቅድ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በማህበረሰቡ ተሳትፎ፣ በጠንካራ የስራ ባህልና በየደረጃው ያለው አመራር ተናቦ በመስራት ረገድ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡
በ2017 በመልካም አስተዳደር፣ በኮሪደር ልማት፣ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋትና ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ 95 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡
በቀጣይም በዚህ አመት የታዩ ጉድለቶችን እንዲሁም አልፎ አልፎ በየዘርፉ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችና የስራ መጓተቶችን በማረምና እጥረቶችን በግልፅ ተወያይቶ መፍትሄ ማበጀት ላይ በትኩረት መስራት በየደረጃው ካለው አመራር ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ አመት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የገበያ ማዕከላትን የበለጠ በማስፋፋት፣ የንግድ ሱቆችና ሼዶችን በመገንባትና ተኪ ምርቶችን በማምረት እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ማቃለል ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በቀጣዩ በጀት አመት ለ350 ሺህ ዜጎች ቋሚና ዘላቂ የስራ ዕድል ይፈጠራል ያሉት ከንቲባዋ፥ የኮሪደር ልማት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ሰላምና ፀጥታ፣ የተቋማት ግንባታ፣ የቤቶች ልማትና መሰል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት፡፡
የህዝቡን የመልማት ፍላጎት ከግምት በማስገባት ሁሉንም ታሳቢ ያደረጉ መሰረተ ልማቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በቅድስት አባተ