Fana: At a Speed of Life!

የሆርቲካልቸር ዘርፍን ምርታማነት የሚያሳድግ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሆርቲካልቸር ዘርፍን ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)።

ብሄራዊ የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ እና የእንሰት ልማት ፍላግሺፕ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የሆርቲካልቸር ዘርፍ የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ እና ለሥራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፥ የዘርፉን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የመሠረተ ልማትና ሎጂስቲክስ እጥረት፣ የተሻሻለ ቴክኖሎጂ አለመኖር እንዲሁም የምርት አያያዝና የግብይት ውስንነት የዘረፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

አዲሱ ብሄራዊ የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመቅረፍ ጥራት ያለው ምርት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር ምርት እምቅ አቅም መኖሩን ጠቁመው፥ በቀጣይ አቅሙን በሚገባ ለመጠቀም እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ስትራቴጂው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣም የዘርፉ ተዋንያን በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ የእንሰት ምርትን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይበልጥ ለማሳደግ እሴት ከመጨመር ጀምሮ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.