አረንጓዴ አሻራ እና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለትውልድ የሚሻገሩ ወረቶች ናቸው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አረንጓዴ አሻራ እና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለትውልድ የሚሻገሩ ወረቶች ናቸው አሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) እና የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርዓያ ሥላሴ፡፡
የመከላከያ፣ የፍትህና የሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።
በተጨማሪም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍና ለአቅም ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ አስጀምረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረትን በማስተካከል፣ በአፈር ጥበቃ እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው።
በዚህ ረገድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርዓያ ሥላሴ በበኩላቸው፥ አረንጓዴ አሻራ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ትልቅ ሚና እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በርስ በመደጋገፍ የተሻለ ነገን ለመገንባት ያስችላል ያሉት ሚኒስትሮቹ፥ ሁሉም ዜጋ በአረንጓዴ አሻራና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለትውልዱ የሚሻገር አሻራ በማኖር የተሻለች ሀገር እየገነባንበት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡