የባህር ዳርን ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት ለማጠናከር በጋራ መትጋት ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባህር ዳር ከተማ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ መትጋት ይገባል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደርና የጣና ዳር ልማትን፣ የመንገድ ግንባታ እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምቹ የሥራ ከባቢ የመፍጠር እንቅስቃሴን ተመልክተናል ብለዋል።
የከተማዋን ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሰፋፊ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተፋጠኑ መሆኑን ጠቅሰው፥ እየተከናወኑ የሚገኙት እነዚህ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ወደ ምቹ እና ዘመናዊነት ምዕራፍ እያሸጋገሯት እንደሆነ አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው እንዳሉት፥ የከተማዋ ማህበረ-ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዕለት ከዕለት እየጨመረ ሲሆን፥ ነዋሪዎቿም ቀን ከሌሊት ህይወት ቀያሪ ሥራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ብርቱ የሥራ ክንዶች ባህርዳርን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገሯት ነው ያሉም ሲሆን፥ የከተማዋ አድባር የሆነው ጣና በተደረገለት የዳርቻ ልማት ውበቷን ይበልጥ እያደመቀ በተከፈቱለት ገላጣ ሥፍራዎች ነፋሻ አየርን እየለገሳት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
ባህርዳር የአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ እንደመሆኗ የክልሉ ተቋማት የከተማዋን ሁሉን አቀፍ ሽግግርና ዘመኑን የዋጀ የተቋማት ግንባታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በቢሮ እድሳት አስደናቂ ለውጥ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እየተፋጠኑ የሚገኙ ሥራዎች ሁነኛ አብነት ናቸው ሲሉ ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የጠቀሱት።
በከተማዋ የተመለከትናቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡