የሀዋሳ ከተማን 2ኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በቅርቡ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የመጀመሪያ ዙር ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የኮሪደር ልማት ስራው ያለበትን ደረጃ በዛሬው ዕለት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ የኮሪደር ልማት ስራውን በፍጥነትና በጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት ከፍት ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ በቅርብ ክትትል እየተሠራ ነው።
የስራ ኃላፊዎቹ ጉብኝት የኮሪደር ልማት ስራው ያለበትን አሁናዊ ደረጃ ለመገምገም ያለመ መሆኑን የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
በምልከታው በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ፣ የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሬ እና የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ ተገኝተዋል።
በኃይለማርያም ተገኝ