Fana: At a Speed of Life!

ፓርቲዎች ለሰላምና ዴሞክራሲ ባህል መዳበር ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዘላቂ ሰላምና ለዴሞክራሲ ባህል መዳበር ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል አሉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ሰላምን በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ አስጀምረናል ብለዋል።

ለኢትዮጵያውያን ሰላም ማለት ልማትን፣ ነጻነትን፣ ፍትሕንና ደስታን ያለ ማንም ዕንቅፋትነት ማግኘት እንደሆነ ገልጸዋል።

በሀገራችን ታሪክ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሰላማችንን ሲነሡን ኖረዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህ ጋብ ሲሉ ደግሞ ግጭት፣ ጦርነትና መፈናቀል ሰላማዊ ሕይወታችንን ይበጠብጡታል ሲሉ አንስተዋል።

እስካሁን ድረስ ለሁለቱም የሚሆን ሁነኛ መፍትሔ አለመበጀቱን እና በዚህም ለድህነትና ለኋላ ቀርነት ተጋላጭ አድርጎናል በማለት ጠቅሰዋል።

ለሁለቱም ምላሽ የሚሰጥ አካሄድን መከተል የለውጡ ዋናው ስትራቴጂ መሆኑን አመልክተዋል።

ዓባይን ገርተን ለኃይል ማመንጫ እንደተጠቀምነው፤ ነፋሱን ገርተን ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እንዳዋልነው፤ የተፈጥሮን ጉልበተኝነት ገርተን ለልማትና ለብልጽግና ማዋል አለብን ብለዋል።

ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን ያዳበረ ሕዝብ እና ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን ያዳበሩ ልሂቃን እንደሚፈልግ ገልጸው፤ የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ ባህል መገንባት እና ለኢትዮጵያውያን ባህልና ዕሴት የሚስማማ ዴሞክራሲን በጋራ መቀመር ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የፓርቲዎች ፉክክር ብቻ ሳይሆን ትብብርም እንደሚያስፈልግ አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን በመቀበል ላበረከቱት አዎንታዊ ሚና ምስጋና አቅርበዋል።

ሰላም የጋራ ሥራ ውጤት በመሆኑ ሰላም ወዳዱ ሕዝብ እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍል መሪዎች፣ የፖለቲካ ኃይሎች መንግሥት ለሰላም ያለዉን ቁርጠኝነት በመረዳት ሰላምን ለማምጣትና ለማጽናት በሚደረገዉ ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.