Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም 162 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት 162 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም በበጀት ዓመቱ የገቢ ምንጭን በማስፋት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

በዓመቱ 162 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው ÷ በዚህም የእቅዱን 99 በመቶ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸርም የ73 በመቶ እድገት ማሳየቱን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ÷በዚህም ተጨማሪ 68 ነጥብ3 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር ከባለፈው ዓመት 6 ነጥብ 2 በመቶ መጨመሩን ጠቁመው÷ የሕዝብ ሽፋኑም 99 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል፡፡

365 ምርትና አገልግሎቶች ለደንበኞች የቀረቡ ሲሆን÷ ከእነዚህ ውስጥም 134ቱ አዳዲስ፤ 157 የሚሆኑት ደግሞ ማሻሻያ የተደረገባቸው ናቸው፡፡

የሳይበር ሴክዩሪቲን ለመከላከልም የተለያዩ ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበር መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

በበጀት ዓመቱ 462 ሺህ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መደረጉን ጠቅሰው ÷ በተገነባው የሳይበር ሴክዩሪቲ አሰራርም ሙከራዎችን ማክሸፍ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.