በቴሌ ብር ከ4 ነጥብ 9 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ተፈጸመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቴሌ ብር መተግበሪያ እስካሁን ከ4 ነጥብ 9 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ተፈጽሟል አሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፡፡
ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 512 ከሞች የ4 ጂ እንዲሁም 16 ከተሞች ደግሞ የ5ጂ ኔትዎርክ አገልግሎት ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
1 ሺህ 683 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች መተከላቸውን ጠቅሰው÷ በዚህም የኔትወርክ አገልግሎትን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ዲጂታል ፋይናንስን በማጠናከር ቀልጣፋ እና ዘመኑን የዋጀ ተደራሽና አካታች አገልግሎት ለመስጠት መሰራቱንም አመልክተዋል፡፡
በ2 ሺህ 388 ቀበሌዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽ መደረጉን ጠቁመው÷ በዓመቱ 5 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
በቴሌ ብር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በማነቃቃት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ÷ በአሁኑ ወቅት የቴሌ ብር ደንበኞች ቁጥር 54 ነጥብ 8 ሚሊየን ደርሷል ነው ያሉት፡፡
በበጀት ዓመቱ በቴሌ ብር 2 ነጥብ 3 ትሪሊየን የገንዝብ ዝውውር መደረጉን ገልጸው÷ አሁን ላይ የቴሌ ብር የገንዘብ ዝውውር 4 ነጥብ 9 ትሪሊየን ብር ደርሷል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ