ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የምግብ ስርዓት ሽግግርን ማዕከል ያደረጉ ተግባራት አከናውናለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግልፅ ስትራቴጂና ፖሊሲዎችን በመቅረጽ የምግብ ስርዓት ሽግግርን ማዕከል ያደረጉ ተግባራት አከናውናለች አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገር በቀል ምርቶችን በማበረታታት ከውጭ ገበያ የሚገቡ ምርቶችን መተካት፣ አነስተኛና መካከለኛ አርሶ አደሮችን በመደገፍ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ የምግብ ስርዓት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ከሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ስርዓቱ ጋር በማጣጣም በተከናወኑ ተግባራት የተመዘገቡ ለውጦችን አብራርተዋል።
የምግብ ስርዓቱ አካታችና ዘላቂ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ እየተገበረችው የሚገኘው የምግብ ስርዓት ፖሊሲ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ነው ብለዋል።
በተለይም በስንዴ ልማት ራስን ከመቻል አልፎ ለውጭ ገበያ እስከማቅረብ የሄደችበትን ርቀት አስረድተዋል።
የዜጎች የአመጋገብ ስርዓት እንዲሻሻል፣ የተመጣጠነ የምግብ ስርዓትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት እንዲሁም በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከገጠር እስከ ከተማ የተገኘውን ውጤት አብራርተዋል።
በሰቆጣ ቃል ኪዳን እና ሌሎችም ውጥኖች የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የተከናወኑት ተግባራት የሚሊየኖችን ህይወት ስለማሻሻላቸው ነው ያነሱት።
የገጠር ልማትና ግብርናውን ለማሻሻል ፍትሀዊ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲዳረስ፣ የገጠር የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማስፋፋትና የአርሶ አደሮችን የአየር ትንበያ ግንዛቤ ለማሳደግ መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
በምግብ ስርዓቱ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የአርሶ አደሮችን የገበያ እሴት ሰንሰለት በማሻሻል ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
ዜጎች ከልጅነት እስከ እውቀት የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት ኖሯቸው ጤንነታቸው የተጠበቀና ስኬታማ እንዲሆኑ በትምህርት ቤት ምገባ ሚሊየኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንዳሉት፥ በአረንጓዴ አሻራ እስካሁን በጥቅሉ ከ46 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ፋይዳዎች ያሏቸው ችግኞች ተተክለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥና ራስን ለመቻል፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ የሥራ እድል በመፍጠር ያመጣውን ለውጥ አብራርተዋል።
አፍሪካ ከማንም ሳትጠብቅ ራሷን የመመገብ አቅም አላት በማለት ገልጸው፥ ይህ እውን እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻዎች በቅንጅት መስራት አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮቿና ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት በመስራት የዓለም የምግብ ስርዓት አሁን ካለበት ስጋት እንዲወጣ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ምግብ የዓለምን ሚዛን የመቆጣጠር ኃይል ያለውና የሰው ልጆችን ህይወት አቅጣጫ የሚወስን ቢሆንም አሁን ላይ በዓለም ላይ ያለው የምግብ ስርዓት በርካታ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈ በዓለም ላይ ያለው የባለብዙ ወገን ትብብር ከፍተኛ ስጋት ውስጥ በመሆኑ የዓለም የምግብ ስርዓት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ጫና አንስተዋል።
በመሳፍንት ብርሌ