Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ለባህልና ስፖርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የላቀ ስኬት ተመዝግቧል – ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 22፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ለባህልና ስፖርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የላቀ ስኬት ተመዝግቧል አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፡፡

“ባህል ጥበባት እና ስፖርት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ግምገማ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በበጀት ዓመቱ የታቀዱ አበይት ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፥ ለአብነትም ኪን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ብስራት ማሳያ በሚል የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ የሚያሳይ የኪነ ጥበብ ቡድን በዓለም ዙሪያ ዝግጅቱን እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ባህልና ቋንቋን በመሰነድ ረገድ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ኪነጥበብ ለሀገር ልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል ከ54 ሺህ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውንም አንስተዋል፡፡

ከ9 ዓመት በኋላ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች መከናወን፣ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር እና ተቋርጠው የነበሩ የስፖርት ፕሮጀክቶች ዳግም መጀመራቸው በስፖርቱ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡

አደይ አበባ ስታዲየምን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው፥ በበጀት ዓመቱ ከ5 ሺህ በላይ የስፖርት ማዘውተሪያዎች በመላ ሀገሪቱ መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በግምገማ መድረኩ ላይ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችና የስፖርት ፌዴሬሽን አመራሮች ተሳታፊ ናቸው።

በበላይነህ ዘለዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.