በሚዲያዎች መካከል የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር አስችሏል
አዲስ አበባ ሐምሌ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በሚዲያዎች መካከል እየተፈጠረ የመጣው ቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር አስችሏል አሉ።
የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ፎረም የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አመራሮች እና ባለሙያዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
አቶ ኃይሉ አዱኛ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሀገሪቱ እየተመዘገበው ላለው የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ የሚዲያው ሚና የላቀ ነው ብለዋል።
ይህንን ሚና ይበልጥ ለማጎልበት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ፎረም ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በፎረሙ አማካኝነት በሚዲያዎች መካከል የተፈጠረዉ ቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር አስችሏል ነው ያሉት።
በ2017 በጀት ዓመት በፎረሙ ተይዘው ከነበሩት ተልዕኮዎች መካከል በመረጃ ልውውጥ፣ ስኬትን በመተንተን፣ ሀሰተኛ መረጃን በመከላከልና በጋራ ትርክት ግንባታ ዙሪያ በተሰሩ ስራዎች ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።
የ2018 በጀት ዓመት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ስራዎች ዕቅድ መነደፉን ገልጸው፥ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር፣ የሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት እንዲሁም አሰባሳቢ የጋራ ትርክት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በዮናታን ብርሃኑ