ለጋዜጠኛ ብርሃኑ ወ/ሰማያት የድጋፍ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምርመራ ዘገባ መሀንዲሱ ተብሎ የሚጠራው ጋዜጠኛ ብርሃኑ ወ/ሰማያት ባጋጠመው ህመም የድጋፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ጋዜጠኛው ያለበትን ሁኔታ ጨምሮ አጠቃላይ የህክምና ሂደቱን አስመልክቶ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው መግለጫ ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ ብርሃኑ ወ/ሰማያት ጠንካራ የሙያ ሰው ላመነበት እውነት እስከ ህይወት መስዋዕትነት የሚከፍል፤ ብልሹ አሰራሮችን አደባባይ በማውጣት ለመልካም አስተዳደር የታገለ ጋዜጠኛ ነው፡፡
ብርሃኑ በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ፋና ሬዲዮን ጨምሮ በበርካታ ተቋማት በሙያው ሀገሩንና ህዝብን በታማኝነት አገልግሏል።
አሁን ላይ ይህ ብርቱ ሰው ሁለቱ ኩላሊቶቹ ስራቸውን በማቆማቸው ከሚወደው ስራ ርቆ ይገኛል፡፡
በዚህም ጋዜጠኛው ያለበት ሁኔታ አፋጣኝ ህክምና እንደሚያስፈልገው ኮሚቴው አስታውቋል።
ጋዜጠኛ ብርሃኑ ሁለቱም ኩላሊቶቹ ስራ ያቆሙ ሲሆን የኩላሊት ንቅለ ተከላ እስኪደረግለት ድረስ በአሜን ሆስፒታል የህክምና ክትትል እያደረገ ነው፡፡
ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በአስቸኳይ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ መታከም እንዳለበት የተነገረው ሲሆን ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ ህክምናውን ለማድረግም ለኩላሊት ንቅለ ተከላው ብቻ ከ50 ሺህ ዶላር በላይ ያስፈልገዋል፡፡
ብርሃኑ ከህመሙ ድኖ ዳግም ወደሚወደው የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲመለስ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ እና ህይወቱን እንዲታደግ ጥሪ ቀርቧል።
በሳራ ስዩም