የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሰራተኞች በወንዶ ገነት ከተማ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሄዱ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሰራተኞች መትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ቃል በሲዳማ ክልል ወንዶ ገነት ከተማ ኖሌ ተራራ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አዶኒያስ ወልደአረጋይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከተቋም ተልዕኮ በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
የአረንጓዴ አሻራ እና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ሀገር ከተጀመረ አንስቶ ተቋሙ በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በቤት ዕድሳት አገልግሎቶች ላይ መሳተፉን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ እና የቤት ዕድሳት መርሐ ግብርም የተቋሙ ሀገራዊ እና ማህበራዊ ኃላፊነት አካል መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የተቋሙ አመራሮች እና ሰራተኞች የበጎ ፈቃድና የአረንጓዴ አሻራ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የወንዶ ገነት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አማካሪ አቶ ስጦታ በገየ በበኩላቸው፥ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አመራርና ሰራተኞች ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖራቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ወንዶ ገነት ከፍተኛ የተፈጥሮ ደን እና የተመጣጠነ ተፈጥሮ ስነ ምህዳር ያላት ከተማ መሆኗን ገልጸው፥ በዛሬው ዕለት የተተከሉ ችግኞች ለከተማዋ ተጨማሪ ገፅታን የሚያላብሱ ናቸው ብለዋል።
እንደ ከተማ አስተዳደር በአንድ ጀንበር 18 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱንም ነው የገለጹት፡፡
በሚኪያስ አየለ