Fana: At a Speed of Life!

ለሀገራችን ማንሰራራት ዐሻራችንን ማኖር ይጠበቅብናል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በርካታ ዜጎች እንዲሳተፉ በማድረግ ለሀገራችን ማንሰራራት ዐሻራችንን ማኖር ይጠበቅብናል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ በአንድ ጀንበር ችግኝ የመትከል ዘመቻን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የታቀደው ግብ እንዲሳካ መላው ህዝብ ሊሳተፍ ይገባል ሲል አስገንዝቧል።

በዚህም ዜጎች ዐሻራቸውን ሊያኖሩ እንደሚገባ በመግለጽ ጥሪ አቅርቧል።

አገልግሎት ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

በመትከል ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ሀገራዊ ጥሪ እንሰለፍ!

በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ በሀገራችን የተረጋጋ ሀገርና ትውልድ ለመገንባት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት መርሃ ግብሩ ከተበሰረ ወዲህ በተለያዩ ዘርፎችም መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡

የሀገራችን የደን ሽፋን መጠንም በፍጥነት እየተቀየረ መጥቷል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የታጀበው ሰባት ዓመታትን የተሻገረ የአትዮጵያ ብልጽግና ጉዞም በሀገራችን ከፍተኛ ውጤቶችን ከማሳየት ባለፈ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ተቋማት ተጽኖ ፈጣሪነት ደረጃዋን ከፍ አድርጎታል፡፡

በመርሃ ግብሩ የዕድሜ፣ የፆታ፣ የብሔር፣ የሃይማኖትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይስተዋሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሕብረተሰብ ክፍሎች በስፋት በመሳተፍ አይተኬ ተሳትፎ አድርጓል፡፡

በሂደቱም መላው ሕዝባችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግና ለውጤት ለማብቃት ባደረገው የጋራ ርብርብ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ ያሳካነውን እምርታ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ከቆምንና ከተባበርን ተዓምራዊ ስራዎችን መከወን እንደምንችል ያሳዩ ናቸው፡፡

የኑሮ መሠረታችን አረንጓዴ ተክሎች መሆናቸውን ሕዝባችን ከመረዳት ባለፈ በተግባር አስመስክሯል፡፡

በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ከ40 ቢሊየን የሚልቁ ችግኞችን እንደ ሀገር ታቅዶ ተተክሏል፤ በዘንድሮ ክረምትም 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

የተተከሉ ችግኞች የማህበረሰቡ የባለቤትነት ስሜትን እና ለአካባቢው ሃላፊነትን እየጎለበቱ በመምጣቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ፣ የአፈር መሸርሸርን ከመቀነስ፣ የደን ሽፋንን ከማሳደግ፣ ለአየር ሚዛን ጥበቃ እና ሕይወት ላለው ሁሉ ለመኖር ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ለአካባቢና ሀገር ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አበርክቶ እያደረገ ይገኛል፡፡

ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአንድ ቀን 700 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል በዚህ ክረምት ለማሳካት የታቀደውን 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ግብ እውን እንድናደርግ ዐሻራችንን እንድናኖር ለመላው ኢትዮጵያዊያን ጥሪ ቀርቧል።

ስለሆነም መላ ሕዝባችን ከሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኝ በመትከል የታቀደውን ግብ እንድናሳካ ሀገራዊ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በሁሉም ሀገራችን ክፍሎች በርካታ ዜጎች እንዲሳተፉ በማድረግ ለሀገራችን ማንሰራራት ዐሻራችንን ማኖር ይጠበቅብናል፡፡

ይህንን ስናደርግ የሀገራችን የተፈጥሮ ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነታችንን እናረጋግጣለን፡፡

ለቀረበው ታሪካዊና ሀገራዊ ጥሪ ተግባራዊነት በመዘጋጀትና ምላሽ በመስጠት የኢትዮጵያን መንሰራራት ጅምር እውን በማድረግና የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበትን አስተዋጾኦ እንዲያበረክት መንግስት ዳግም ጥሪውን ያቀርባል።

በመትከል እናንሰራራለን!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.