ኢትዮጵያዊነት ብያኔዉ የተሻለ ዓልሞ የላቀ ማሳካት ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያዊነት ብያኔው የተሻለ ዓልሞ የላቀ ማሳካት ነው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
አገልግሎቱ በዛሬው ዕለት በሀገር አቀፍ ደረጃ በስኬት የተጠናቀቀውን የአንድ ጀንበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔ መነሻ፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል ብቻ አይደለችም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያ የመጪው ትውልድ የተስፋ ምድር ጭምር ናት ሲል አውስቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን ደግሞ በጋራ ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባሻገር የሚገለጹና የመቻል ተምሳሌቶች መሆናቸውን ነው ያስገነዘበው፡፡
ለአብነትም ኢትዮጵያውያን “በጋራ እንችላለን” መነንፈስ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እውን ማድረጋቸውን ጠቅሷል፡፡
“በጋራ ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብስ” በማለት ኢትዮጵያውያን ላለፉት ስድስት ዓመታት ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል መንከባከባቸውን አስታውሷል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ብያኔው የተሻለ ዓልሞ የላቀ ማሳካት ነው ያለው አገልግሎቱ ÷የአንድ ጀንበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ኢትዮጵያዊነት ብያኔዉ የተሻለ ዓልሞ የላቀ ማሳካት ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔ መነሻ፣ የጥቍር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል ብቻ አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የመጪዉ ትውልድ የተስፋ ምድር ጭምር ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በጋራ ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባሻገር የሚገለጹ፣ የመቻል ተምሳሌቶች ናቸው፡፡
“በጋራ እንችላለን” ብለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እውን አደረጉ፡፡ “በጋራ ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብስ” ብለው ላለፉት ስድስት ዓመታት ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተከሉ፤ ተንከባከቡ፡፡
ለዓለም ንጹሕ አየርን አበረከቱ፤ ወደፊትም ያበረክታሉ፡፡ በዚህ ኢትዮጵያውያን የመቻል ምልክቶች ኾነናል፡፡ በስኬቶቻችንም ኢትዮጵያዊነትን ለእኛ ኩራት፤ ለብዙዎች ምኞት ማድረግ ችለናል፡፡
በአንድ ጀምበር በርካታ ችግኞችን የመትከል ክብረ ወሰንን፣ በየዓመቱ እየሰባበሩ ዐዳዲስ ታሪኮችን መጻፍ የቀጠሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የኮሮና-ቫይረስ ወረርሽኝ ቢሊዮኖችን በቤት ውስጥ አስቀምጦ ኢትዮጵያውያን ግን ነገን በማለም ችግኝ ይተክሉ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ሰላሟ ታውኮ፣ እየተዋጉ ሰላሟን እንደሚያጸኑ ተማምነው፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ ችግኞችን ይተክሉ ነበር፡፡ መትከል ብቻ ሳይኾን የራሳቸዉን ስኬት በሌላ ስኬት ያሻሽሉት፣ ያሳድጉት ነበር፡፡ እነኾ ዛሬም የራሳቸዉን ክብረ ወሰን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ አደረጉት፤ በአንድ ጀምር ከዐቀዱት በላይ ችግኞችን በመትከል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብያኔዉ የተሻለ ዓልሞ የላቀ ማሳካት ነው፡፡
የዛሬዉም ኾነ ያለፉት ዓመታት ድሎች ግን እንዲሁ የተገኙ አይደሉም፡፡ የችግኝ ማፍያ ቦታዎችን የማዘጋጀት፣ ችግኞችን የማፍላት፣ መትከያ ቦታዎችን የመለየትና የማዘጋጀት፣ ችግኞችን በወቅቱ የመትከል እና የመንከባከብ አድካሚ ጥረትን ይጠይቃሉ፡፡
ነገር ግን ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሲተጋገዙ፤ መንግሥትና ሕዝብ ሲቀናጁ፣ ስለነገዋ ኢትዮጵያ የጋራ ተስፋ ሰንቀው ሲጥሩ፣ … የሚቻሉ ኾነዋል፡፡ ይህንን ላደረጉ ኢትዮጵያውያን ኹሉ ምስጋና ይገባል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባስተላለፏቸዉ ጥሪዎች ኹሉ ከፊት የሚገኙ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣ ዛሬም የሀገራቸዉን ሕልም በማሳካት ዐዲስ ታሪክ ጽፈዋል፡፡
በዛሬዋ ዕለት ከ29 ሚሊዮን 700 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ የሚገኙ ዲፕሎማቶች እና ተቋማት ኃላፊዎች ችግኞችን ተክለዋል፡፡ በዕለቱ 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ቢታቀድም በጥረታቸዉ ካለሙት በላይ የሚያሳኩት ኢትዮጵያውያን ከ714 ሚሊዮን 700 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል ሌላ የከፍታ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡
ከዓድዋ ድል እና ከሕዳሴ ግድብ ስኬት ዕኩል የምንመለከተዉ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብራችን፣ በዘንድሮዉ ክረምት ብቻ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮችን ችግኞችን የምንተክልበት ትልቅ ንቅናቄ ነው፡፡
ዛሬ ያሳካነውን ድል ብዙ ሀገራት ሊያልሙት ይችሉ ይኾናል፤ የምናሳካዉ ግን በጋራ ስንቆም አንዳች ኃይል የማይበግረን ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን! በየዓመቱ ክብረ ወሰኖቻችንን ራሳችን ብቻ እያሻሻልን መቀጠላችን ለዚህ ምስክር ነውና፡፡
ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊ መኾን፣ ለኛ ኩራት ለብዙዎች ምኞት ነው የምንልው፡፡ በድጋሜ ይህንን ድል ያሳካችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ደስ አለን፤ ደስ አላችሁ! ላደረጋችሁት የጋራ ጥረት ኢትዮጵያ ታመሰግናችዋለች! ጥሪዉን ተቀብላችሁ፣ ዝናብና ብርድ ሳይበግራችሁ፣ የኢትዮጵያን መሻት በላቀ ደረጃ ስላሳካችሁ መንግሥት በእጅጉ ያመሰግናችኋል!
ኢትዮጵያውያን ኹሉንም ማድረግ በጋራ እንችላለን!
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም