ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ከ118 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 118 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፡፡
የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የኤሌክትሪክ ሃይል ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኃይል ማመንጨት ሥራ ላይ በትኩረት በመሥራት ለውጪ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል የማቅረብ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይም ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል እየሸጠች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 25 ሺህ በላይ ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 29 ሺህ በላይ ጊጋ ዋት ሰዓት ማመንጨት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከተመረተው ኃይል ውስጥም ለኬንያ 85 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ ለማከናወን ታቅዶ 86 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ለጅቡቲና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ በቅደም ተከተል 30 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር እና 900 ሺህ ዶላር መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ከሶስቱ ሀገራት በተጨማሪ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ በሙከራ ደረጃ መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡
ለጎረቤት ሀገራቱ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሽያጭም በአጠቃላይ 118 ነጥብ 1ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ካመረተው ሃይል ውስጥ 7 በመቶውን ወደ ውጪ በመላክ ከተቋሙ አጠቃላይ ገቢ 20 በመቶ የሚሆነውን መሸፈን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ