Fana: At a Speed of Life!

የባህር በር የሌላቸውን ሀገራት ተሳትፎ የሚገድበው የንግድ ስርዓት መሻሻል አለበት – አንቶኒዮ ጉተሬዝ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የባህር በር የሌላቸውን ሀገራት ተሳትፎ የሚገድበው ኢ-ፍትሃዊ የዓለም የንግድ ስርዓት መሻሻል አለበት አሉ፡፡

3ኛው የተባበሩት መንግስታት በማደግ ላይ ያሉ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ጉባኤ በቱርክሜኒስታን በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በተለያዩ አህጉራት በማደግ ላይ ያሉ ከ30 በላይ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በርካታ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን በመጋፈጥ ላይ ናቸው፡፡

የባህር በር አልባ መሆን የሀገራትን የንግድ እንቅስቃሴ ገደብ ሊበይን አይገባም ያሉት ዋና ጸሀፊው፥ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ እንዲዳረጉና በዓለም የንግድ ስርዓት በአግባቡ እንዳይሳተፉ እያደረጉ ያሉ ገደቦች እንዲነሱ አሳስበዋል፡፡

እነዚህ ሀገራት ከአጠቃላይ የዓለም ህዝብ 7 በመቶ ያህሉን እንደሚይዙ ጠቅሰው፥ ነገር ግን በዚህ ገደብ ምክንያት በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፏቸው ከ1 በመቶ የዘለለ አይደለም ነው ያሉት፡፡

አንቶኒዮ ጉተሬዝ በንግግራቸው ይህ ኢፍትሃዊ የዓለም ንግድ ስርዓት ከዛሬዋ የተሳሰረች ዓለም እውነታዎች ጋር ያልተጣጣመ ያለፈው የቅኝ ግዛት ዘመን ውርስ ነው ሲሉ ነቅፈዋል፡፡

የጉባኤው ዋና ዓላማ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የንግድ ስርዓትን ማንበርና የባህር በር በሌላቸው ሀገራት የመልማት እድሎች ላይ ያለውን ገደብ ማንሳት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክም በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.