በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ የተከሰሱበትን ስልጣንን አላግባብ መገልገል ወንጀል ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተለያየ የስራ ኃላፊነት ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ የተከሰሱበትን ስልጣንን አላግባብ መገልገል ወንጀል ክስ እንዲከላከሉ ብይን ሰጠ፡፡
ተከሳሾች 1ኛ አቶ ሙልዬ ወለላው የፌዴሬሽን ም/ቤት የህገ-መንግስት ትርጉምና የሕጎች ሕገ መንግስታዊነት ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበረ፣ 2ኛ አቶ ኃ/ሚካኤል ልኬ የህግ አማካሪ እና ጠበቃ፣ 3ኛ አቶ ቃላት ባህታ በግል ስራ የሚተዳደርን ጨምሮ 7 ግለሰቦች ናቸው፡፡
በመጀመሪያ ክስ በ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) (ሀ) እና (2) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ነው፡፡
1ኛ ተከሳሽ በፌዴሬሽን ም/ቤት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የስራ መደቦች እና ኃላፊነቶች ላይ ሲሰራ ከ2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር የማይገባቸውን ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ለሌሎችም ለማስገኘት በማሰብ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተከስቶ የነበረውን የድንበር ግጭት ተከትሎ የሀገር ደህንነትን እና ህልውናን ለማስጠበቅ ሲባል ከሀገር የተሸኙ ኤርትራዊያን ንብረቶችን በጨረታ እንዲሸጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ከሀገር እንዲወጡ በተደረጉት ኤርትራዊ ቦሌ ክ/ከ ወረዳ 3 ስር የሚገኝ መኖርያ ቤት እና ይዞታ ለጨረታ እንዲቀርብ ተደርጎ 1ኛ የዐቃቢ ህግ ምስክር ወ/ሮ አልጋነሽ ኃይሉ የጨረታው አሸናፊ በመሆን በ1992 ዓ.ም የሽያጭ ውል በመፈፀም ቤቱን ከተረከቡ በኋላ ተከሳሾች በሀሰተኛ ደብዳቤው መነሻነት በዜግነት ኤርትራዊት የሆነችው 4ኛ ተከሳሽ ኢትዮጵያዊ ናት በሚል መደምደሚያ ላይ በመድረስ ውሉ ፈርሶ ቤቱን የዐቃቢ ህግ ምስክር የሆነችው ወ/ሮ አልጋነሽ ኃይሉ ኤርትራዊት ለሆነችው 4ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ኤልሳቤት ተስፋጽዮን እንድታስረክብ በማለት የፌዴሬሽን ም/ቤት የወሰነውን ውሳኔ ድጋሚ ለምክር ቤቱ እንዳይቀርብ ለማድረግ በአካልና በስልክ በመገናኘትና በመደራደር፣ የዐቃቢ ህግ 1ኛ ምስክር ብር 400 ሚሊየን የሚገመት ቤትን እንዲያጡ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት ስልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ዘርዝሯል።
በሁተለኛ ክስ በተመሳሳይ1ኛ፣ 2ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ከላይ በዝርዝር በተገለጸው የወንጀል ድርጊታቸው በህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ በአብላጫው ድምጽ ትርጉም አያስፈልገውም በማለት በመወሰኑ በውሳኔው ቅር በመሰኘት የህገ-መንግስት ትርጉም ይሰጥልኝ ሲሉ ሕገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጣቸው ለፌዴሬሽን ም/ቤት የዕግድ እና የይግባኝ አቤቱታ በም/ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ ውሳኔው እንዳይቀየር በማድረግ ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት እና የግል ተበዳዮችን ቤትን እና ይዞታን በማሳጣት የግል ተበዳዮች 1 ሺህ ካሬ ሜትር ቤትና ይዞታን እንዲያጡ በማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ ጉዳት በማድረሳቸው፣ 1ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች በመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ብቻ በሚፈጸም የሙስና ወንጀል ውስጥ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ከሆኑት 2ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የከባድ የስልጣን አላግባብ መገልገል ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በሶስተኛ ክስ በ1ኛ እና 7ኛተከሳሾች 1ኛ ተከሳሽ በተጨማሪነት ለራሱም የማይገባውን ብር 200 ሺህ ብር በማግኘቱ 1ኛ ተከሳሽ በመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ብቻ በሚፈጸም የሙስና ወንጀል ውስጥ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ከሆነው 7ኛ ተከሳሽ ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት በከባድ ስልጣንን አላግባብ መገልገል ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት 3ኛ ተከሳሽ በቂ ማስረጃ ስላልተገኘበት በነፃ ተሰናብቷል።
4ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች በሌሉበት ጥፋተኛ ሲባሉ ቀሪዎቹ ተከሳሾች ክሱን እንዲከላከሉ ለሕዳር 2 እና 3 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በሲፈን መኮንን